Welcome

In the name of the Father, the Son and the Holy Spirit; one God. Amen

Repent for the kingdom of God is near Matthew 3፥2, Mark 1፥2, Luke 3፥3

Repent for it is near that heaven for being a child, being a child through faith shall be given

Dear readers, welcome to the website of the first, by God’s grace, John the Baptist EOTC church in North America named Hamere Berehan Kidus Yohannes Metmik EOTC. For those who strove to make this a reality, I say glory be to God.

የሐመረ ብርሃን ቅዱስ ዮሐንስ ቤተ ክርስቲያን እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ ያነሳሳቸው ካህናት፣ ምዕመናንና ምዕመናት ተሰባስበው ሲመካከሩ ከቆዩ በኋላ ቤተ ክርስቲያን ለመትከል በመወሰናቸው በቀኖና ቤተ ክርስቲያን መሠረት በብፁዕ አቡነ ፋኑኤል የዲሲና ካሊፎርኒያ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ፈቃድ የተተከለ ነው፡፡ ቤተ ክርስቲያኑ የተተከለው በሜሪላንድ ግዛት በሞንትጎሞሪ ክልል ማለትም በራክቪል፣ ጌተርስበርግ፣ ኦልኒ፣ ጀርመን ታውን፣ ክላርክስበርግ፣ ፖቶማክ፣ ሲልቨርስፕሪንግ፣ ወዘተ. አካባቢ የሚገኙ ምዕመናን በቦታ ርቀት ምክንያት ወደ ሌሎች አብያተ ክርስቲያናት ለመሄድ ባለመቻላቸው መንፈሳዊ አገልግሎት እንዲያገኙና የምሥጢራት ተሳታፊ እንዲሆኑ ለማድረግ ነው፡፡

ሐመር/መርከብ አማናዊት ቤተ ክርስቲያን ናት፡፡ የክርስቶስ አካል የሆኑትን ልጆችዋን ማለትም ሕዝበ ክርስቲያንን ማዕበል፣ ሞገድና ነፋሳት ከበዛበት ዓለም ባህር አጓጉዛ ገነት መንግሥተ ሰማያት ታደርሳለችና፡፡ ብርሃን የተባለውም መድኅነ ዓለም ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፡፡ ስለዚህ ቤተ ክርስቲያናችን ሐመረ ብርሃን ቅዱስ ዮሐንስ መጥምቅ ተብሎ ተሰይሟል፡፡

ቅዱስ ዮሐንስ መጥምቅ በመለአኩ በቅዱስ ገብርኤል ብሥራት በሰውና በእግዚአብሔር ፊት ጻድቃን ተብለው ከሚታወቁት ከካህኑ ከዘካርያስና ከኤልሳቤጥ የተወለደ ሲሆን በወንጌል እንደተጻፈው መንግሥተ ሰማያት ቀርባለችና ንስሐ ግቡ፡፡ የእግዚአብሔርን መንገድ አዘጋጁ፤ ጥርጊያውንም አስተካክሉ እያለ በምድረ በዳ ያስተምር ነበር፡፡ ማቴ. ፫ ፥ ፪ መጥምቁ ዮሐንስ በነብዩ በኢሳይያስ አስቀድሞ ቃለ ዓዋዲ ዘይሰብክ በገዳም፤ በምድረ በዳ የሚያስተምር የአዋጅ ነጋሪ ቃል ኢሳ. ፲፩ ፥ ፩ ተብሎ የተነገረለት ነው፡፡ በዚያን ጊዜ በይሁዳ፣ በኢየሩሳሌምና በዮርዳኖስ አውራጃ ያሉ ሰዎች ሁሉ ወደ እርሱ ይሄዱ ነበር፡፡ ኃጢአታቸውንም እየተናዘዙ ሁሉም በዮርዳኖስ ወንዝ ይጠመቁ ነበር፡፡ ማቴ. ፫ ፥ ፮

ከሰዱቃውያንና ከፈሪሳውያን ወገን መጥተው ሲጠመቁ አይቶ እናንተ የእፉኝት ልጆች ከሚመጣው ቁጣ ትሸሹ ዘንድ ማን አመለከታችሁ? እንግዲህስ ለንስሐ የሚያበቃችሁን በጎ ሥራ ሥሩ፡፡ አብርሃም አባት አለን በማለት የምታመልጡ አይምሰላችሁ ………ምሳር በዛፎች ግንድ ላይ ሊቆርጥ ተዘጋጅቷልና መልካም ፍሬ የማያፈራ ዛፍ ሁሉ ይቆረጣል፤ ወደ እሳትም ይጣላል፡፡ ማቴ. ፫ ፥ ፱ ጥምቀቱንም በተመለከተ እኔ ለንስሐ በውኃ አጠምቃችኋለሁ፤ ከእኔ በኋላ የሚመጣው እሱ ከእኔ አስቀድሞ የነበረ ነው ከእኔ ይበልጣል፤ እርሱ በእሳት ያጠምቃችኋል፤ የጫማውን ጠፍር ልፈታ አይገባኝም፡፡ ማቴ. ፫ ፥ ፲፩ እያለ ያስተምር ነበር፡፡

ቅዱስ ዮሐንስ በብሕትውና በበረሃ/በገዳም የኖረ፣ የብሉይና የሐዲስ መሸጋገሪያ፣ የመጨረሻው ነቢይና የመጀመሪያው ሐዋርያ ነው፡፡ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስም ከሴቶች ከወለዷቸው ወገን ከመጥምቁ ዮሐንስ የሚበልጥ አልተነሳም  ማቴ. ፲፩ ፥ ፲፩ ተብሎ በጌታ የተመሰከረለት ነው፡፡

ቅዱስ ዮሐንስ መጥምቅ ከዕረፍቱ በኋላ ብዙ ቃል ኪዳን የተሰጠው መሆኑ በገድሉ በሰፊው ተጽፎ ይገኛል፡፡ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ምዕመናንም በየቦታው በቃል ኪዳኑ ሲጠቀሙ በመኖራቸውና እየተጠቀሙ በመገኘታቸው ቋሚ ምስክር ናቸው፡፡ በነፍስም በሥጋም ብዙዎች ፈውስን አግኝተዋልና፡፡

እኛም በዚህ በትንቢቱ ፍጻሜ ዘመን ላይ የምንገኝ በሐመረ ብርሃን ቅዱስ ዮሐንስ መጥምቅ ቤተ ክርስቲያን አማካይነት የሚከተሉትን መንፈሳዊ አገልግሎት ለመስጠትና ሐዋርያዊ ተልዕኳችንን ለመወጣት ጥረት እናደርጋለን፡፡ እነዚህም፦

  1. ወንጌልን በመስበክ ኃጢአት በሰለጠነበት በዚህ ዘመን ይልቁንም ሥጋዊውን ፍላጎት ለሟሟላት እየባከነ በኃጢአትና በበደል ርቆ ያለውን ሁሉ በንስሐ ሕይወት መጥራትና ለሥጋ ወደሙ ማብቃት፤
  2. በንስሐ ለሥጋ ወደሙ የበቃውንም ምግባር ትሩፋትን በመሥራት ሃይማኖቱን በተግባር የሚገልጽ ክርስትናን በሕይወቱ የሚያስተምር እንዲሆን መርዳት፤
  3. እንደ ቅዱስ ዮሐንስ ሁሉም ዓይነት የሰው ዘር በቀለም፣ በቋንቋ ሳይለዩ ሃይማኖት አልባ የሆነ ያለውን ዓለም ጥቁር አና ነጭ አሜሪካዊ፣ ኢትዮጵያዊ፣ ወዘተ በማስተማር ሀብተ ወልድና ስመ ክርስትና እንዲያገኝ ማድረግ፤
  4. ካህናትም ሆነ ምዕመናን የእውነት ምስክርነት የሚሰጡ፤ እውነትን ሳይፈሩና ሳያፍሩ እንዲመሰክሩ፤ እንዲገስጹ፤ በይሉኝታና በውዳሴ ከንቱ ሳይጠራሩ ለቤተ ክርስቲያንም ሆነ ለሀገራችን የእውነት ምስክሮች እንዲሆኑ ማድረግ፤
  5. ሕዝበ ክርስቲያኑ ነፍሱን እንዲያድን በሃይማኖትና በሥነ ምግባር ታንጾ እንዲኖር፤ ትውልዱ ኦርቶዶክሳዊ የተዋሕዶ ሃይማኖትን እንዲኖረውና ኦርቶዶክሳዊነት በዓለም እንዲስፋፋ ማድረግ
  6. ሕጻናትና ወጣቶች ሃይማኖታቸውን፣ ሥርዓታቸውን አውቀው እንዲረከቡ ማድረግ
  7. በእግዚአብሔር ህግ በቀኖና ወይም በህገ ቤተ ክርስቲያን የምትመራ፣ በቃለ ዓዋዲ መሠረት የምትደዳደር፣ ግልጽና ዘመናዊ አወቃቀር፣ አደረጃጀትና አሠራር ያላት የአጥቢያው ቤተ ክርስቲያን በመመሥረት አብነት የሚሆኑ ተግባራትን ማከናወን
  8. ቅዱስ ዮሐንስ መጥምቅ ባለው ቃል ኪዳን በሥጋ ቁስልና ደዌ በመንፈስና በአጋንንት አሽክላ ተይዘው ለሚሰቃዩ ወገኖች የጸበል አገልግሎት መስጠት
  9. ለትምህርተ አበ ነፍስ ትኩረት በመስጠት በተለይም የምክር አገልግሎት መስጠት

ውድ አንባብያንና በመላው ዓለም የምትገኙ የቤተ ክርስቲያን ልጆች ይህች የተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በጌታ መንገድ ጠራጊና ቃለ ዓዋዲ ተብሎ በተጠራው በቅዱስ ዮሐንስ ስም ተሰይሞ የእግዚአብሔር ቃል በመዝራት ዘርና ቀለም ሳይለይ እንዲድን፤ መንፈሳዊ አገልግሎቱን የፈጽማል። ይልቁንም ተተኪው ትውልድ ሃይማኖቱን እንዲረክብ የሚደረገውን ጥረት በጸሎትም ሆነ በሚቻላችሁ ሁሉ ድጋፍ እንድታደርጉልን አደራ እንላለን፡፡

May the blessings of John the Baptist be upon us. Amen.

Glory be to God

Melake Tsion Kesis Belachew Worku

Administrator of the Church