ቅበላ የኅሊና ዝግጅት ወይስ?

ይህንን ጽሑፍ በ2007ዓ.ም በwww.eotcmk.org ለንባብ ያበቃሁት ሲሆን ዛሬም ሰሞነኛ ሆኖ መጥቷልና መልካም ንባብ።

ቅበላ ማለት የጾም ዋዜማ ፣ጾም ከመግባቱ በፊት ቀደም ብሎ ያለው ቀን ወይም ሰሞን ማለት ነው፡፡ በአትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ሥርዓትና ትውፊት መሠረት ሰንበታት፣ አጽዋማትና በዓላት በዋዜማው በጸሎት (በምኅላ)፣በመዝሙር፣በትምህርት ወዘተ. ልዩ አቀባበል ይደረግላቸዋል ፡፡

ለምሳሌ አይሁድ ሰንበትን(ቅዳሜ) ሲያከብሩ በዋዜማው አቀባበል ያደርጉላታል፡፡

ዓርብ ፀሐይ ሲገባ ካህኑ ደውል ይደውላሉ አሊያም በቤት ያለ የቤቱ አባወራ የሰንበት መግቢያ ሰዓት መቃረቡን ድምጽ በማሰማት ያሳውቃል፡፡ በአካባቢው ያሉ ሁሉ ይሰበሰባሉ፡፡ በአንድ ላይ ሆነው ወደ ፀሐይ መውጫ ይሰግዳሉ፡፡ ጸሎት ይደረጋል፡፡ ይትባረክ እግዚአብሔር አምላከ እስራኤል፣አሥርቱ ቃላት ሌሎችም ንባባት ይደገማሉ፡፡ ማብራት ተይዞ “ዕለተ ሰንበት እንኳን ደህና መጣሽ” ብለው ያከብሯታል፡፡ ከሦስት ሰዓት በኋላ እራት ይበላሉ፡፡ ሌሊቱን በሙሉ እግዚአብሔርን ሲያመሰግኑ ያድራሉ፡፡

አይሁድ(በሀገራችን ቤተ እስራኤላዊያንም) የፋሲካን በዓል ከማክበራቸው በፊት የሰባት ቀን ጾም ይጾማሉ፡፡ በዋዜማው(ቅበላ) ይሆናል፡፡ በኦሪት ዘጸአት12፡5 ከግብጽ ባርነት ነጻ ስለመውጣታቸው እንደተጠቀሰው ለፋሲካ ጾም አቀባበል ያደርጋሉ፡፡ነውር የሌለበት የአንድ ዓመት ተባዕት ከበጎች ወይም ከፍየሎች ወስደው በወሩ እስከ አሥራ አራተኛው ቀን ድረስ ጠብቀው የእስራኤል ማኅበር ጉባኤ ሁሉ ሲመሽ ያርዱታል፡፡ ከደሙም ወስደው በሚበሉበት ቤት መቃኑና ጉበኑን ይቀቡታል።በእሳት የተጠበሰውን ሥጋውንና ቂጣውን እንጀራ በዚያች ሌሊት ይበላሉ ከመራራ ቅጠል ጋር ይበሉታል።ጥሬውንና በውኃም የበሰለውን አይበሉም፡፡ … የቀረ ቢኖር በእሳት ያቃጥላሉ ፡፡ያልቦካ ቂጣ ይበላሉ፡፡

ይህንን አድርገው መጻሕፍት ያነባሉ፣ጸሎት ያደረጋሉ፡፡ በጾማቸው ወቅት ተጠንቅቀው ጾመው ይጨርሱና የፋሲካን በዓል ያከብራሉ፡፡

ይህ ሁሉ ለሀዲስ ኪዳን ምሳሌ ነበር፡፡ጾሙን የመሠረተልን ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፡፡ የፋሲካው በግም እርሱ ነው፡፡ነጻ ያወጣንም ከዲያቢሎስ አገዛዝ ነው፡፡

ቅበላ በተለይ የነነዌ ጾም እንዳለቀ ዐቢይ ጾም /ጾመ ሁዳዴ መስከረም አንድ ቀን በታወጀው መሠረት ቀናት ሲቀረው መናንያን፣ ካህናትና ምእመናን ጾሙን ለመቀበል የተለያዩ ዝግጅቶች ያደረጋሉ፡፡ ጾሙ አባ ዲዮስቆሮስ ስለ ዐቢይ ጾም ታላቅነት “ከመ እንተ ብእሲ ለጸዊም በውስተ ገዳም ኃደረ። እምኀበ ዲያብሎስ ተመከረ በኃይለ መለኮቱ መኳንንተ ጽልመት ሠዓረ፤ እንደ ሰው ሆኖ ለመጾም ፵ መዓልት ፵ ሌሊት በገዳመ ቆሮንቶስ ኖረ። ከዲያብሎስ ዘንድ በሦስት አርእስተ ኃጣውዕ ተፈተነ፥ ድል ይነሣልን ዘንድ። ፭ ሺህ ከ፭ መቶ ዘመን ሰልጥነው የኖሩትንና የጨለማ ገዥ የሆኑትን ሠራዊተ ዲያብሎስን በጌትነቱ ሻረልን።” እንዳለው ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን አብነት አድረገን በመጾም በዚህ ዓለም ስንኖር ጥንተ ጠላት ዲያቢሎስን ድል ለማድረግ፣በጾሙ በረከት፣ ጸጋና መንፈሳዊ ኃይል ለማግኘት እንድንበቃ የምናደርገው የዝግጅት ሰሞን ነው፡፡

በቅበላ ሰሞን አባቶቻችን በየገዳማቱና አድባራቱ ለቤተ እግዚአብሔር መገልገያ የሚሆኑ ንዋያትንና መብዓ ያዘጋጃሉ፡፡ስምንቱን የዐቢይ ጾም የሱባዔ ሳምንታት የሚያሳልፉበትን ቦታ ይመርጣሉ፡፡ ለጸሎት የሚያግዟቸውን መጻሕፍት ያዘጋጃሉ፡፡

በጾም፣ በጸሎት፣ በምጽዋት ለማሳለፍ ዕቅድ ያወጣሉ፡፡ ጥሉላት(የእንስሳትና የዓሣ ሥጋ፣የእንስሳት ውጤቶች) ምግቦችን ካስፈለጋቸው ለህሊናቸው ዕረፍት ለመስጠት በመጠኑ ይመገባሉ ጾመው ለማበርከትና ዋጋ ለማግኘት፡፡ በከተማና በገጠር የሚገኙ ምእመናንም ጧፍ፣ዕጣን፣ዘቢብ ፣አልባሳት ሲገዙ ይሰነብታሉ፡፡ አልፎ አልፎም ጾሙን በንጹህ ህሊና ለመጀመር ከአበ ነብሳቸው ጋር ይወያያሉ፡፡ “ወኢትፍራሕ ተጋንዮ በእንተ ኃጢአተከ ኃጢአትህን ለማመን ለመናገር አትፍራ፡፡” እንዳለ ሲራክ 3፡18፡፡ የበደሉ ማሩኝታ የተጣሉም ይቅርታ ይጠይቃሉ ፡፡ ነግቶ ለኪዳን፣ ቀኑን ለቅዳሴና ለሠርክ ጸሎት ለማወል ያቅዳሉ፡፡ መዝሙር ቤቶችም የበገናና ዘለሰኛ መዝሙራትን ያሰማሉ፡፡

ዛሬ ዛሬ ግን ቅበላ ሲባል በአብዛኛው አዕምሮ የሚከሰተው ከሰባው አርዶና አወራርዶ አሊያም ልኳንዳ ቤት ተሰልፎና ታድሞ፣ጥሉላት ምግቦችን በዓይነት አሰልፎ፣ ጠጅ (አልኮል) ተጎንጭቶ፣ከመጠን ያለፈ ደስታ ፈጥሮ ጾሙን መቀበል ሆኗል፡፡ ቅዱስ ጴጥሮስም በመልእክቱ 1ኛጴጥ 5፡8 “በመጠን ኑሩ ንቁም፥ ባላጋራችሁ ዲያብሎስ የሚውጠውን ፈልጎ እንደሚያገሣ አንበሳ ይዞራልና” እንዳለው ከመጠን ያለፈ ማንኛውም ደርጊት ለፈተና ብሎም በዲያቢሎስ ሊያስማርከን ይችላል፡፡

አንድ መምህር ሲያስተምር የሰማሁት ሴትየዋ በቅበላ ብዙ የጥሉላት ምግቦችን አዘጋጅታ ስትመገብ ሰንብታ ጾሙ ሲገባ ምግቡ ሳያልቅ ይቀራል፡፡ አላስችል ብሏት በጾሙ የመጀመረያ ሳምንት የተረፈውን ምግብ ትመገባለች፡፡

ይህችን እናት የህሊና ወቀሳ እረፍት ነሳት ለአበ ነብሷ(ለንስሀ አባቷ) መንገር ጥሩ አማራጭ እንደሆነ ተረድታ ያደረገችውን ነገረቻቸው፡፡ አበ ነብሷም አስተምረው ቀሪውን ጾም በተገቢው ሁኔታ እንድትጾም መክረው ይሸኟታል፡፡ ጾሙ ሊያልቅ ሲቃረብ “ክፉ ባልንጀርነት መልካሙን አመል ያጠፋል።” እንዳለ ቅዱስ ጳውሎስ 1ቆሮ 15፡33 ከማይጾሙ ጓደኞቿ ጋር በመዋሏ የጥሉላት ምግብ ትመገባለች፡፡ አሁንም ከህሊና ወቀሳ መዳን ስላልቻለች ለአበ ነብሷ ለመናገር ወስና ነገረቻቸው፡፡አበ ነብሷም የሴትየዋን ስም ጠርተው “ምነው! ጾሙ ሲገባ አላስገባ አሁን ሊወጣ ሲል አላስወጣ አልሽ ፡፡ ”አሏት ይባላል፡፡

ጾም አቀባበል የሚደረግለት መንፈሳዊነትን ባለቀቀ መልኩ በመጠኑ ሲሆን፤በመጾማችን ድል የምናደርግበት፣በመንፈስ የምናድግበት፣የቤተክርስቲያን ልጅነታችንን የምናረጋግጥበት(ቀኖናና ሥርዓቷን ስለምንጠብቅ) ይሆናል፡፡

ስለዚህ ዝግጅታችን ምን ይሁን?

ጾሙን ተቀብለን፤ ጾመን፣ጸልየን፣መጽውተን ሰግደን ዋጋ እንድናገኝ እግዚአብሔር ይርዳን።

ጥር 26ቀን 2010ዓ.ም

መምህር ቀሲስ ሳሙኤል ተስፋዬ

የጥምቀት ከተራ በዓል አከባበር የትመጣ

ይህን ጽሑፍ ጥር 9 ቀን 2006 ዓ.ም በማኅበረቅዱሳን ድረ-ገጽ/ www.eotcmk.org አውጥቼው የነበረ ሲሆን አሁን መጠነኛ ማስተካከያ ተደርጎበታል፡፡

ከተራ ከበበ ካለው የግእዝ ግሥ የወጣ ነው፡፡ ፍችው ውኃ መከተር፣ መገደብ ማለት ነው፡፡ የጥምቀት ዋዜማ ታቦተ ሕጉ ከቤተ መቅደስ ወጥቶ ውኃ ባለበት አካባቢ ስለሚያድር የየአጥቢያው ሕዝብ እየተሰበሰበ በወንዝ ዳር ወይም በምንጭ አካባቢ ድንኳን ይተከላል፡፡ ድንኳንም ከሌለ ዳስ ሲጥል ይውላል፡፡ የምንጮች ውኃ ደካማ በመሆኑ እንዲጠራቀም ይከተራል ጉድጓድ እየተቆፈረ ውኃው እንዳይሄድ ይገደባል፡፡

“ከተራ” በመባል የሚታወቀው – ዋዜማው” ሠርግው /1981፣8/ እንደገለጹት “ከተራ” የሚለው ቃል “ከተረ ከበበ ካለው የግዕዝ ግስ የወጣ ነው፡፡ ከተራ ፍቺውም ውኃ መከተር፣ ወይም መገደብ ማለት ነው፡፡” ብለው ሲፈቱ፣ ደስታ ተከለ ወልድ /1962፣ 694/ ደግሞ የጥምቀት ዋዜማ፣ ጥር 10 የጠራ ወራጅ ውኃ የሚከተርበት ታቦትና ሰው ወደ ዠማ ወንዝ የሚወርዱበት ጊዜ” ነው በማለት ይፈቱታል፡፡

ኪዳነ ወልድ ክፍሌም /1948፣ 555/ ከተረ የሚለውን ቃል በቁሙ፣ “ዘጋ፣ አቆመ፣ አገደ፣ ከለከለ፡፡” ማለት ነው ብለው ይፈቱታል፡፡ በየዓመቱ ጥር 10 ቀን የምእመናኑ አብዛኛው ሥራ ውኃውን መከተርና መገደብ በመሆኑ ዕለቱ ከተራ የሚል ስያሜ ተሰጥቶታል፡፡ ውኃው የሚከተረው በማግሥቱ ጥር 11 ቀን የጥምቀት በዓል ስለሚከበር ለሕዝቡ መጠመቂያ እንዲሆን ነው፡፡ በየሰበካው ቦታ ተለይቶና ተከልሎ ታቦታቱ በዳስ ወይም በድንኳን የሚያድሩበት፣ የተለያዩ የውኃ አካላት ተጠርገው የሚከተሩበት ወይም ሰው ሠራሽ የግድብ ውኃ የሚበጅበት ስፍራ ‹‹ባሕረ ጥምቀት››፣ ‹‹የታቦት ማደርያ›› እየተባለ ይጠራል፡ ባሕር፡- የውኃ መሰብሰቢያ (ምእላደ ማይ፣ የውኃ መከማቻ (ምቋመ ማይ) ነው፡፡ በሌላ አነጋገር ‹‹የውኃ አገር›› /መካነ ማይ፣ ዓለመ ማይ/ ነው፡፡

የቀደሙ አባቶቻችን በተለይ በቅዱስ ላልይበላ ዘመነ መንግሥት በኢትዮጵያ ምድር እየተመላለሱ በብሕትውና እና በስብከተ ወንጌል ያገለግሉ የነበሩት ጻድቁ አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ በአክሱም፣ በመቐለና በመርጡለ ማርያም እየተዘዋወሩ ባሕረ ጥምቀቱን ባርከዋል፡፡

በዐፄ ይኩኖ አምላክ ዘመነ መንግሥት (1260-1275 ዓ.ም) በጻድቁ አቡነ ተክለ ሃይማኖት (1203-1204 ዓ.ም) አሳሳቢነት የተጀመረው ሥርዐተ በዓል ተጠናክሮ እንዲቀጥል በዐዋጅ ትእዛዝ አስተላልፈዋል፡፡ ታቦታቱም በሕዝብ ጥበቃና ክብካቤ ተደርጎላቸው በየጥምቀተ ባሕሩ እንዲያድሩ ወስነዋል፡፡

የበዓሉ አከባበር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየሰፋና አድማሱ ብሔራዊነትን እየያዘ መጣ፡፡ ከዐፄ ገብረ መስቀል ጀምሮ የአደባባይ በዓል የሆነው የጥምቀት በዓል በ15ኛው ክ/ዘመን በደገኛው ኢትዮጵያዊው ንጉሠ ነገሥት ዐፄ ዘርዓ ያዕቆብ(1426-1460 ዓ.ም) አማካኝነት ታቦታቱ ወደ ወንዝ ወርደው ዕለቱን እንዳይመለሱ፣ በዚያ ፈንታ በጥምቀት ዋዜማ ጥር 10 ቀን ከሰዓት በኋላ ወደ ባሕረ ጥምቀቱ ወርደው እንዲያድሩ፣ አገሩን በኪደተ እግር ይባርኩም ዘንድ በሄዱበት መንገድ እንዳይመለሱ በዐዋጅ ወሰኑ፡፡ ይህን ታሪክ በመከተል ዐፄ ናዖድ (1486-1500) ዓ.ም) ማንኛውም የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ሃይማኖት ምእመን ታቦተ ሕጉ ወደ ባሕረ ጥምቀቱ በሚወርድበት እና ከባሕረ ጥምቀቱ ወደ ቤተ መቅደሱ በሚመለስበት ጊዜ አጅቦ አውርዶ፣ አጅቦ መመለስ እንዳለበት በዐዋጅ አስነግረው ነበር፡፡

ሕዝቡም ታቦታተ ሕጉን በሆታና በእልልታ ከቤተ መቅደስ አጅቦ ከአወጣ በኋላ በባሕረ ጥምቀት ከትሞ ማደር ጀመረ ።/ሐመር ጥር/የካቲት 1998 ዓ.ም/ ታቦታት ከአንድ በላይ ሆነው ወደ ከተራው ስለሚሄዱ እግዚአብሔር አምላክ ለነብዩ ሙሴ “የታቦት መኖር ከእናንተ ጋር የመኖሬ ምልክት ነው” ዘፀ 25÷1 እንዳለው ታቦተ ሕጉን ተሸክመው ዮርዳኖስን እንደ ተሻገሩት ካህናተ ኦሪት፤ ካህናቱ የማይለወጠውን ታቦተ ሕጉን በራሳቸው ተሸክመው የብሉዩን ሥርዓት ከሐዲስ ኪዳን ጋር አንድ አድርገው የሐዲስ ኪዳን መሠረት ኢየሱስ ክርስቶስን እያሰቡ፤ ካህናተ ሐዲስም ወደ ከተራ (ዮርዳኖስ) ይጓዛሉ፡፡

ሊቃውንቱም ለበዓሉ የሚስማማውን ቃለ እግዚአብሔር እያደረሱ ያድራሉ። የከተራ ዕለት ጥር 10 ቀን ኢየሱስ ክርስቶስ በዮሐንስ እጅ ለመጠመቅ ከገሊላ ወደ ዮርዳኖስ ወንዝ የሄደበትን ለማዘከር ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን ኃዳፌ ነፍስ ለጻድቃን የሚለውን ዋዜማ ይቆማሉ፡፡ የዋዜማው ቀለም ከቀኑ በአራት ሰዓት በመላው አጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት ይጀመራል ከዚያም የዋዜማው ሥርዐት ቅዱስ ተብሎ እስከ ሰላም ያለው ቀለም ይደርሳል፡፡

በዕለቱም ቅዳሴ ይቀደሳል፡፡ ታቦተ ሕጉን የሚያነሡት ሰሞነኛ ካህን ከምግበ ሥጋ ተከልክለው ለዕለቱ የሚገባውን ጸሎት ያደርሳሉ፡፡ በከተራው ዕለት ድንኳን ተተክሎ፣ ዳሱ ተጥሎና ውኃው ተከትሮ ሁሉም ነገር ከተስተካከለ በኋላ ታቦተ ሕጉ የሚንቀሳቀስበት ሰዓት ሲደርስ የየቤተ መቅደሱ ታቦታት በወርቅና በብር መጎናጸፊያ እየተሸፈኑ በተለያየ ኅብር በተሸለሙ የክህነት አልባሳት በደመቁ ካህናትና የመጾር መስቀል በያዙ ዲያቆናት ከብረው፣ ከቤተ መቅደስ ወደ አብሕርት /ምጥማቃት/ ለመሄድ ሲነሡ መላው አብያተ ክርስቲያናት የደወል ድምፅ ያሰማሉ፡፡ ምእመናን ከልጅ እስከ ዐዋቂ በዐጸደ ቤተ ክርስቲንና ታቦታቱ በሚያልፉባቸው መንገዶች ‘’ለጥምቀት ያልሆነ ቀሚስ …’’ እንደሚባለው ያማረ ልብሳቸውን ለብሰው በዓሉን ያደምቃሉ፡፡ የበዓሉን ሂደት ታቦቱ ከመንበረ ክብሩ ሲነሳ ‹‹ዮም ፍስሀ ኮነ›› ተብሎ ከተጸነጸለ በኋላ ታቦቱ ወጥቶ ወረደ ወልድ እምሰማያት ውስተ ምጥማቃት የሚለው ሰላም በሊቃውንቱ ይዘመራል፣ ይጸነጸላል፣ ይመላለሳል፡፡

የወርቅ ካባና ላንቃ የለበሱ ቀሳውስት፣ መነኮሳት ጥላ የያዙት ከታቦቱ ጎን መስቀልና ጽና የያዙት ከታቦቱ ፊት ይሄዳሉ፡፡ እንደ ቀሳውስቱ ተመሳሳይ ልብሰ ተክህኖ የለበሱት ዲያቆናት ጥላ፣ መስቀልና ቃጭል ይዘው እያቃጨሉ ከቀሳውስቱ ፊት በመሆን ያጅቧቸዋል፡፡ ከነዚህም ሌላ ካባ፣ ላንቃ ጥንግ ድርብ የለበሱ መዘምራን የብር፣ የነሐስ መቋሚያና ጸናጽል ይዘው ‹‹ወረደ ወልድ›› የሚለውን አመላለስ እያሸበሸቡ ዲያቆናቱን ቀድመው ይሄዳሉ፡፡ የደብር አለቆችና አበው ካህናት ታቦቱን ተከትለው ይጓዛሉ፡፡ የሰንበት ት/ቤት ተማሪዎችም በተለያዩ ቀለማት ባሸበረቁ አልባሳት ተውበው ትርዒት እያሳዩ “ወረደ ወልድ፣ እግዚኡ መርሐ፣ ሆረ ኢየሱስ” እና ሌሎችንም የአማርኛ መዝሙራትን እየዘመሩ፣ እናቶች “ነይ ነይ እምዬ ማርያም” እያሉ ሌሎችም ምስጋናዎችም እየቀረቡ ጉዞ በዝግታ ወደ ጥምቀተ ባሕር ይሆናል፡፡ የከተራ በዓል ማክበሪያ ቦታ እንደደረሱ ታቦታቱ በድንኳኑ አጠገብ ቆመው ‹‹ወረደ ወልድ›› የሚለው ሰላም ተመርቶ በአግባቡ ከተለዘበ በኋላ ጸሎት ተደርጎ የዕለቱ ትምህርተ ወንጌልና ዝማሬ ከቀረበ በኋላ ውዳሴ ማርያም፣ መልክዐ ኢየሱስ ተደግሞ ታቦታ ሕጉ ወደ ተዘጋጀላቸው ድንኳን ይገባሉ /ሠርግው፤ 1981፣ 9/፡፡

በሁለተኛ የአገልግሎት ክፍል ካህናቱ ስብሐተ እግዚአብሔር ሲያደርሱ ያድራሉ፡፡ በመንፈቀ ሌሊትም ሥርዐተ ቅዳሴው ተጀምሮ ከሌሊቱ በ9፡00 ሠርሆተ ሕዝብ ይሆናል፡፡ በነጋታው የሥርዐተ ጥምቀቱ መርሐ ግብር ይቀጥላል፡፡ የከተራ በዓል ምሳሌያት በበዓለ ጥምቀት ዋዜማ የታቦታቱ ወደ ወንዝ መውረድና የባሕረ ጥምቀቱ መዘጋጀት ሃይማኖታዊ ታሪክና ምሳሌ አለው፡፡

የቃል ኪዳኑን ታቦት አክብሮ መጓዝና ወደ ወንዝ መወረድ የተጀመረው በአሮን ልጅ በአልዓዛር ጊዜ ነው፡፡ ኢያሱ በሙሴ እግር ተተክቶ ሕዝበ እስራኤልን እየመራ ከዮርዳኖስ ወንዝ ሲደርስ ባሕሩ ከሁለት ይከፈልና ወራጁም ይቆም/ይከተር/ ነበር፡፡ እስራኤል ዘሥጋ ወደ ምድረ ርስት ለመግባት የዮርዳኖስን ወንዝ ሲሻገሩ፡- ድንኳን ጥለው የቃል ኪዳኑን ታቦት በድንኳን ውስጥ አድርገው ሌዋውያኑ በዙሪያው፣ ካህናቱ ደግሞ በውስጥ ኾነው እግዚአብሔርን እያመሰገኑ አድረው በማለዳ ተሻግረዋል /ኢያሱ 3÷8-9/፡፡

ካህናቱ የቃል ኪዳኑን ታቦት አክብረው የወንዙን ዳርቻ በረገጡት ጊዜ እንደ ክረምት ማዕበል ይወርድ የነበረው ውኃ ግራና ቀኝ ተከፍሎ እንደ ግድግዳ ወደ ላይ ቆሟል፡፡ ሕዝቡ ተሻግሮ እስከሚያበቃ ታቦተ ጽዮንን ያከበሩት ካህናት ከወንዙ መሀል ይቆሙ ነበር፡፡ በዚህ መሠረት ‹‹ወተጠምቃ እገሪሆሙ ለካህናት›› ይህም ‹‹የካህናት እግሮቻቸው የዮርዳኖስን ውኃ በመርገጣቸው እንደ ጥምቀት ሆናቸው›› በሐዲስ ኪዳነ ጌታችን ለመሠረተው ሥርዐተ ጥምቀት ምሳሌ ነበር፡፡

ቤተ ክርስቲያናችን የጥምቀትን ዋዜማ ከተራ ብላ የጠራችው ከዚህ በመነሣት ነው፡፡ ጌታችን በተጠመቀ ጊዜ የዮርዳኖስ ወንዝ የላይኛው ሸሽቶ ወደ ላይ ተመልሶ ሽቅብ ፈሷል፡፡ የታቹም ወደ ታች ሸሽቷል፡፡ የላይኛው ፈሳሽ ተቋርጦ እንደ ክምር ተቆልሎ ቀርቷል።ቅዱስ ዳዊት የተመለከተውም ይህንኑ ነው። ከአዳም ጀምሮ እስከ ክርስቶስ ድረስ በዘር ይወርድ የነበረው ፍዳ መርገም በክርስቶስ ቤዛነት ተቋርጦ ፤ የታቹም ፈጽሞ መድረቁ ኃጢአተ አዳም የመጥፋቱ ምሳሌ ነው፡፡ እስራኤል ፈለገ ዮርዳኖስን ተሻግረው ወደ ኢያሪኮ መሔዳቸው ምእመናን በጥምቀት ከኃጢአት ቍራኝነት ተላቀው እግራቸውን ወደ ልምላሜ ገነት ወደ ዕረፍት መንግሥተ ሰማያት አቅንተው ለመሔዳቸው ምሳሌ ነው፡፡ ኢያሱ የጌታ፣ እስራኤል የምእመናን፣ ዮርዳኖስ የጥምቀት፣ ምድረ ርስት የገነት መንግሥተ ሰማያት ምሳሌ ነው፡፡

ታቦቱን አክብሮ የሚሔደው ካህን የቅዱስ ዮሐንስ፣ታቦቱ የጌታችን፣ ባሕረ ጥምቀቱ የዮርዳኖስ ወንዝ፣ ታቦታቱን አጅበው የሚሔዱትና በዓሉን የሚያከብሩት ምእመናን ወደ ቅዱስ ዮሐንስ እየመጡ የንስሐ ጥምቀት ሲጠመቁ የነበሩት ሰዎች ምሳሌዎች ናቸው፡፡ ታቦታቱ በጥምቀት ዋዜማ ከመንበራቸው ወደ ጥምቀተ ባሕር መውረዳቸውና በዚያ ማደራቸው ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በእደ ዮሐንስ በፈለገ ዮርዳኖስ ከማታው ጀምሮ መውረዱንና ተሰልፎ ተራውን ሲጠብቅ ማደሩን ያጠይቃል፡፡ ‹‹ጥምቀት የሞቱና የትንሣኤው ምሳሌ ነው፡፡ ከኃጥአን ጋር ተቆጥሮ እንዲጠመቅና እንዲሰቀል የተጻፈውን ቃል ንስሐና ጥምቀት የማያስፈልገው ሲሆን ነገር ግን ፍጹም ኃጥእ መስሎ በዮሐንስ እጅ ጥምቀትን ለመፈጸም በማየ ዮርዳኖስ እግር ተጠመቀ፡፡›› /ኪ.ወ.ክ ፤517/፡፡

ጌታችን የተጠመቀበት ወርኀ ጥር በእስራኤላውያን ዘንድ የዝናብ፣ የበረዶ ወራት ነው፡፡ ከወንዝ ዳር ያለ መጠለያ መዋልና ማደር አይቻልም፡፡ በመኾኑም ከዮሐንስ ለመጠመቅ የሚሄዱ ሰዎች ሁሉ በዮርዳኖስ ዙሪያ ድንኳናቸውን ተክለው ያርፉ ነበር፡፡ በዚህ አንጻር ዛሬም በባሕረ ጥምቀት ዙሪያ ድንኳኖች ዳሶች ይጣላሉ፡፡ በሀገራችን በተለያዩ አካባቢዎች በተለይ በአክሱም የንግሥት ሳባ መዋኛን ‹‹ማይ ሹም›› በጎንደር የዐፄ ፋሲል መዋኛን፣ በላስታ የላሊበላ መዋኛን፣ በሸዋ የዐፄ ዘርዐ ያዕቆብ ፍርድ መስጫ አደባባይን፣ አርባ አራት ታቦታት የሚያድሩበትን የሸንኮራ ሜዳን “ራቡቴ ወንዝ” በአዲስ አበባ ደግሞ ጃንሆይ ሜዳን /ጃንሜዳን/ ወዘተ ለአብሕርተ ምጥማቃት እንደ ምሳሌ መጥቀስ ይቻላል፡፡ እኒህ ቦታዎች ዛሬም ድረስ ተከብረው ይገኛሉ፡፡እኛ በዚህ ወቅት ታቦት ይዘን፣ ከወንዝ ወርደን፣ ድንኳን ተክለን በማክበራችን ይፈጸማል፡፡

በጥምቀት ከእግዚአብሔር ያገኘነውን ልጅነት ጠብቀን እንድኖር አምላካችን ይርዳን

መ/ር ሳሙኤል ተስፋዬ

ጥር 8ቀን 2010ዓ.ም

ጥምቀት

††† በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን! †††

<<< በዓለ ኤጲፋንያ >>>

††† “ኤጲፋንያ” የሚለው ቃል ከግሪክ (ጽርዕ) ልሳን የተወሰደ ሲሆን በቁሙ “አስተርእዮ: መገለጥ” ተብሎ ይተረጐማል። በነገረ ድኅነት ምሥጢር ግን ኤጲፋንያ ማለት “የማይታይ መለኮት የታየበት: እሳተ መለኮት በተዋሐደው ሥጋ የተገለጠበት” እንደ ማለት ነው።

“ዘኢያስተርኢ ኅቡዕ እስመ አስተርአየ ለነ። እሳት በላዒ አምላክነ።” እንዲል። (አርኬ)

አንድም: ምሥጢር ሆኖ የቆየ አንድነቱ: ሦስትነቱ የተገለጠበት ቀን ነውና ዕለተ ጥምቀቱ ኤጲፋንያ ይሰኛል። መድኃኒታችን ክርስቶስ አዳምንና ልጆቹን ያድን ዘንድ ከሰማያት ዙፋኑ ወርዶ: እንደ ሰውነቱ በሥጋ ማርያም ለ33 ዓመታት ተመላልሷል። ጊዜው ሲደርስም በፈለገ ዮርዳኖስ: ከዮሐንስ ዘንድ ሊጠመቅ ሔደ። መድኃኒታችን ከገሊላ ወደ ዮርዳኖስ የወረደው ጥር 10 ቀን አመሻሽ ላይ ሲሆን በፍጹም ትሕትና ተራ ሲጠብቅ አድሮ ሌሊት 10 ሰዓት ላይ ደረሰውና ሊጠመቅ ቀረበ። አሥር ሰዓት መሆኑም ርግብ (መንፈስ ቅዱስ) ሲወርድ ሰዎች ሥጋዊት ርግብ ናት ብለው እንዳይጠራጠሩ ነው። ርግብ በሌሊት መንቀሳቀስ አትችልምና። መድኃኒታችን ወደ ቅዱስ ዮሐንስ ሲጠጋ አምላክነቱን ተረድቶ “እንዴት ፈጣሪየ ወደ እኔ ትመጣለህ? እንዴትስ በእኔ እጅ ትጠመቃለህ?” አለው። ትህትና ለእናትና ልጅ ልማዳቸው ነውና። ጌታ ግን “ጽድቅን ሁሉ ልንፈጽም ይገባል” ሲል እንዲያጠምቀው ፈቀደለት። ቅዱስ ዮሐንስም “ስመ አብ በአንተ ሕልው ነው። ስመ ወልድ ያንተ ነው። ስመ መንፈስ ቅዱስም በአንተ ዘንድ ሕልው ነው። በማን ስም አጠምቅሃለሁ?” ሲል ጠየቀው። ጌታ “ወልዱ ለቡሩክ ከሣቴ ብርሃን ተሣሐለነ። አንተ ካህኑ ለዓለም በከመ ሲመቱ ለመልከ ጼዴቅ” እያልክ አጥምቀኝ አለው። ትርጉሙም “የቡሩክ አብ የባሕርይ ልጁ : ብርሃንን የምትገልጥ ሆይ ይቅር በለን! አንተ እንደ መልከ ጼዴቅ ሹመት የዓለም ካህኑ ነህና” እንደ ማለት ነው። ከዚያም ጌታ ወደ ዮርዳኖስ ሲገባ ባሕር አይታ ደነገጠች : ሸሸችም። (መዝ. 76:16, 113:3) ዮርዳኖስ ጨንቆት ግራ ቀኝ ተመላለሰ። እሳተ መለኮት ቆሞበታልና ውኃው ፈላ። በጌታ ትዕዛዝ ግን ጸና። ጌታ ተጠምቆ: ሥርዓተ ጥምቀትን ሠርቶ: ዮርዳኖስን ብርህት ማሕጸን አድርጐ: የእዳ ደብዳቤአችንንም ቀዶ ከወጣ በኋላ ሰማያት ተከፈቱ። ማለትም አዲስ ምሥጢር ተገለጠ። አብ በደመና ሆኖ “የምወደው: የምወልደው: ሕልው ሆኜ ልመለክበት የመረጥኩት የባሕርይ ልጄ ይህ ነው!” ሲል በአካላዊ ቃሉ ፍጹም ተዋሕዶን መሰከረ። መንፈስ ቅዱስም በአምሳለ ርግብ ወርዶ በራሱ ላይ ተቀመጠ። ራሱንም ቆንጠጥ አድርጐ ያዘው። በዚህም የሥላሴ አንድነቱ: ሦስትነቱ ታወቀ: ተገለጠ። ቅዱስ ዮሐንስ “መጥምቀ መለኮት” የሚባልበትን ታላቁን ክብር ሲያገኝ ዮርዳኖስ የልጅነት መገኛ ቅዱስ ባሕር ሆነ።

<<< ቅዱስ ዮሐንስ መጥምቅ >>>

ቅዱስ ወንጌል ላይ ቅዱስ ሉቃስ “ዘካርያስ ካህኑና ቅድስት ኤልሳቤጥ በሰውና በእግዚአብሔር ፊት ያለ ነቀፋ የሚኖሩ ጻድቃን ነበሩ” ይላቸዋል። (ሉቃ. 1:6) እሊህ ቅዱሳን ባልና ሚስት ግን መካኖች በመሆናቸው ልጅ ሳይወልዱ ዘመናቸው አልፎ ነበር። እንደ ቤተ ክርስቲያን ትውፊት ዕድሜአቸው የኤልሳቤጥ 90 የዘካርያስ ደግሞ 100 ደርሶ ነበር። ፍጹም መታገሳቸውን የተመለከተ ጌታ ግን በስተ እርጅናቸው ከሰው ሁሉ በላይ የሆነ: ትንቢት ለብቻው የተነገረለት (ኢሳ. 40:3, ሚል. 3:1) ታላቅ ነቢይን ይሰጣቸው ዘንድ መልአከ ብሥራት ቅዱስ ገብርኤልን ላከላቸው። ቅዱስ ዘካርያስ ሰው ነውና ከደስታ ብዛት በመከራከሩ ድዳ ሆነ። ቅድስቲቷ ግን መስከረም 26 ቀን ታላቁን ሰው ጸንሳ ለ6 ወራት ራሷን ሠወረች። በ6ኛው ወር የፍጥረት ሁሉ ጌታ በተጸነሰ ጊዜ የአርያም ንግሥት ድንግል እመቤታችን ደጋ ደጋውን ወደ ኤልሳቤጥ መጣች። ሁለቱ ቅዱሳት የእህትማማች ልጆች ናቸው። የአምላክ እናቱ ስትደርስና “ሰላም” ስትላቸው መንፈስ ቅዱስ በእናትና ልጅ ወርዶ ኤልሳቤጥ በምስጋና: ዮሐንስ ደግሞ ገና በማሕጸን ሳለ በደስታ ዘለለ (ሰገደ)። ከዚህ በኋላ ሰኔ 30 ተወልዶ: አባቱ ዘካርያስ “ዮሐንስ” ሲለው አንደበቱ ተፈትቶለታል።

ቅዱስ ዮሐንስ ከተወለደ 2 ዓመት ከ6 ወር በሆነው ጊዜ ሰብአ ሰገል በመምጣታቸው በእሥራኤል ምድር የሚገኙ ሕፃናትን ሔሮድስ ቁዝ አስፈጀ። ትንሽ ቆይቶም አይሁድ ለሔሮድስ ስለ ቅዱሱ ሕፃን ነገሩት። “ሲጸነስ የአባቱን አንደበት የዘጋ: ሲወለድ ደግሞ የከፈተ ‘ዮሐንስ’ የሚባል ሕፃን አለና እሱንም ግደል” አሉ። እናቱ ቅድስት ኤልሳቤጥ ይዛው ስትሸሽ ካህኑን ዘካርያስን ግን በቤተ መቅደስ መካከል ገድለውታል። አረጋይት ኤልሳቤጥም ሕፃኑን እያሳደገች በገዳመ ዚፋታ ለ3 (5) ዓመታት ቆይታለች። ቅዱስ ዮሐንስ 5 (7) ዓመት ሲሞላው ግን እዚያው በበርሃ እናቱ ዐረፈች። ከሰማይ ዘካርያስና ስምዖን ወርደው ቀበሯት። ሕፃኑ ዮሐንስ ሲያለቅስ ድንግል ማርያም ስንት አገር አልፋ ሰማችው። እርሷም ስደት ላይ ነበረችና። ከጌታ ጋር በደመና ሒደው ድንግል አቅፋ አጽናናችው። ጌታንም “እንውሰደው ይሆን?” አለችው። ጌታችን ግን “ለአገልግሎት እስክጠራው እዚህ ይቆይ” አላት። ባርካው: አጽናንታውም ተለያዩ። ቅዱስ ዮሐንስ ከዚህ በኋላ በዚያ ቆላ የግመል ጠጉር ለብሶ: ጠፍር ታጥቆ ተባሕትዎውን ቀጠለ። ለ25 (23) ዓመታትም በንጽሕና ሲኖር ከምድር አራዊትና ከሰማይ መላእክት በቀር ማንንም አላየም። ይሕችን ዐመጸኛ ዓለምም አልቀመሳትም።

ከዚህ በኋላ 30 ዘመን ሲሞላው እግዚአብሔር ከሰማይ ተናገረው። “ሒድ! የልጄን ጐዳና ጥረግ” አለው። ነቢያት ስለዚህ ነገር ተናግረው ነበርና። (ኢሳ. 40:3, ሚል. 3:1) አባቱ ዘካርያስም “ወአንተኒ ሕፃን ነቢየ ልዑል ትሰመይ: እስመ ተሐውር ቅድመ እግዚአብሔር ከመ ትጺሕ ፍኖቶ” (ሉቃ. 1:76) ብሎ መንገድ ጠራጊነቱን ተናግሮ ነበርና። ቅዱስ ዮሐንስ በዚያ ጊዜ በኃይለ መንፈስ ቅዱስ እየገሰገሰ ከበርሃ ወደ ይሁዳ መጣ። ያዩት ሁሉ ፈሩት: አከበሩት። ቁመቱ ቀጥ ያለ: ጽሕሙ እንደ ተፈተለ ሐር የወረደ: ጸጉሩ የቁራ ያህል የጠቆረ: መልኩ የተሟላ: ግርማው የሚያስፈራ ገዳማዊ ነውና። ፈጥኖም ሕዝቡን ለንስሐ ሰበከ: ለንስሐም በርካቶችን አጠመቃቸው። በዚህ አገልግሎት ለ6 ወራት ቆይቶ ጌታችን ወደ እርሱ ዘንድ መጣ። ዮሐንስ ሰማይን ከነግሱ: ምድርን ከነልብሱ የያዘ ፈጣሪ “አጥምቀኝ” ብሎ ሲመጣ ደነገጠ። የሚገባበትም ጠፋው። “እንቢ ጌታየ! አንተ አጥምቀኝ” አለው። ጌታ ግን “ፈቅጄልሃለሁ” አለው: አጠመቀው። በዚህ ምክንያት ይሔው እስከ ዛሬም “መጥምቀ መለኮት” ሲባል ይኖራል። ቅዱስ ዮሐንስ በመጨረሻ ሔሮድስን ገሰጸው። ንጉሡም ተቀይሞ ለ7 ቀናት አሠረው። ልደቱን ባከበረ ጊዜ ወለተ ሔሮድያዳ በዘፈን አጥምዳ አስማለችው። እርሱም የታላቁን ነቢይ ራስ አስቆርጦ በወጪት አድርጐ ሰጣት። አበው “እምሔሶ ለሔሮድስ ይብላዕ መሐላሁ – ሔሮድስ መሐላውን በበላ በተሻለው ነበር” ይላሉ። የቅዱስ ዮሐንስ ራሱ በርራ ስትሔድ አካሉን ግን ደቀ መዛሙርቱ ቀብረውታል። (ማቴ. 3:1, ማር. 6:14, ሉቃ. 3:1, ዮሐ. 1:6)

=>”አስማተ-ዮሐንስ መጥምቅ /የመጥምቁ ዮሐንስ ስሞች”

 1. ነቢይ
 2. ሐዋርያ
 3. ሰማዕት
 4. ጻድቅ
 5. ካሕን
 6. ባሕታዊ / ገዳማዊ
 7. መጥምቀ መለኮት
 8. ጸያሔ ፍኖት (መንገድ ጠራጊ)
 9. ድንግል
 10. ተንከተም (የብሉይና የሐዲስ መገናኛ ድልድይ)
 11. ቃለ አዋዲ (አዋጅ ነጋሪ)
 12. መምሕር ወመገሥጽ
 13. ዘየዐቢ እምኩሉ (ከሁሉ የሚበልጥ)

=>አምላከ ቅዱሳን በጥምቀቱ ይቀድሰን። ከበረከተ ጥምቀቱም ያድለን።

=>ጥር 11 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ በዓላት

 1. በዓለ ኤጲፋንያ
 2. ቅዱስ ዮሐንስ መጥምቅ
 3. አቡነ ሐራ ድንግል ጻድቅ
 4. አባ ወቅሪስ ገዳማዊ
 5. አባ ዮሐንስ ሊቀ ጳጳሳት
 6. ቅዱስ እንጣልዮስ ሰማዕት

=>ወርኀዊ በዓላት

 1. ቅዱስ ያሬድ ካህን
 2. ማር ገላውዴዎስ ሰማዕት
 3. ቅዱስ ፋሲለደስ ሰማዕት
 4. ቅድስት ሐና ቡርክት

=>”ጌታ ኢየሱስም ከተጠመቀ በኋላ ወዲያው ከውኃ ወጣ። እነሆም ሰማያት ተከፈቱ። የእግዚአብሔርም መንፈስ እንደ ርግብ ሲወርድ: በእርሱ ላይም ሲመጣ አየ። እነሆም ድምጽ ከሰማያት መጥቶ:- ‘በእርሱ ደስ የሚለኝ: የምወደው ልጄ ይህ ነው’ አለ።” (ማቴ. ፫፥፲፮)

††† ወስብሐት ለእግዚአብሔር †††

መጽሐፈ ስንክሳር፣ ከዲ/ን ዮርዳኖስ ማስታወሻ