ይህንን ጽሑፍ በ2007ዓ.ም በwww.eotcmk.org ለንባብ ያበቃሁት ሲሆን ዛሬም ሰሞነኛ ሆኖ መጥቷልና መልካም ንባብ።
ቅበላ ማለት የጾም ዋዜማ ፣ጾም ከመግባቱ በፊት ቀደም ብሎ ያለው ቀን ወይም ሰሞን ማለት ነው፡፡ በአትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ሥርዓትና ትውፊት መሠረት ሰንበታት፣ አጽዋማትና በዓላት በዋዜማው በጸሎት (በምኅላ)፣በመዝሙር፣በትምህርት ወዘተ. ልዩ አቀባበል ይደረግላቸዋል ፡፡
ለምሳሌ አይሁድ ሰንበትን(ቅዳሜ) ሲያከብሩ በዋዜማው አቀባበል ያደርጉላታል፡፡
ዓርብ ፀሐይ ሲገባ ካህኑ ደውል ይደውላሉ አሊያም በቤት ያለ የቤቱ አባወራ የሰንበት መግቢያ ሰዓት መቃረቡን ድምጽ በማሰማት ያሳውቃል፡፡ በአካባቢው ያሉ ሁሉ ይሰበሰባሉ፡፡ በአንድ ላይ ሆነው ወደ ፀሐይ መውጫ ይሰግዳሉ፡፡ ጸሎት ይደረጋል፡፡ ይትባረክ እግዚአብሔር አምላከ እስራኤል፣አሥርቱ ቃላት ሌሎችም ንባባት ይደገማሉ፡፡ ማብራት ተይዞ “ዕለተ ሰንበት እንኳን ደህና መጣሽ” ብለው ያከብሯታል፡፡ ከሦስት ሰዓት በኋላ እራት ይበላሉ፡፡ ሌሊቱን በሙሉ እግዚአብሔርን ሲያመሰግኑ ያድራሉ፡፡
አይሁድ(በሀገራችን ቤተ እስራኤላዊያንም) የፋሲካን በዓል ከማክበራቸው በፊት የሰባት ቀን ጾም ይጾማሉ፡፡ በዋዜማው(ቅበላ) ይሆናል፡፡ በኦሪት ዘጸአት12፡5 ከግብጽ ባርነት ነጻ ስለመውጣታቸው እንደተጠቀሰው ለፋሲካ ጾም አቀባበል ያደርጋሉ፡፡ነውር የሌለበት የአንድ ዓመት ተባዕት ከበጎች ወይም ከፍየሎች ወስደው በወሩ እስከ አሥራ አራተኛው ቀን ድረስ ጠብቀው የእስራኤል ማኅበር ጉባኤ ሁሉ ሲመሽ ያርዱታል፡፡ ከደሙም ወስደው በሚበሉበት ቤት መቃኑና ጉበኑን ይቀቡታል።በእሳት የተጠበሰውን ሥጋውንና ቂጣውን እንጀራ በዚያች ሌሊት ይበላሉ ከመራራ ቅጠል ጋር ይበሉታል።ጥሬውንና በውኃም የበሰለውን አይበሉም፡፡ … የቀረ ቢኖር በእሳት ያቃጥላሉ ፡፡ያልቦካ ቂጣ ይበላሉ፡፡
ይህንን አድርገው መጻሕፍት ያነባሉ፣ጸሎት ያደረጋሉ፡፡ በጾማቸው ወቅት ተጠንቅቀው ጾመው ይጨርሱና የፋሲካን በዓል ያከብራሉ፡፡
ይህ ሁሉ ለሀዲስ ኪዳን ምሳሌ ነበር፡፡ጾሙን የመሠረተልን ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፡፡ የፋሲካው በግም እርሱ ነው፡፡ነጻ ያወጣንም ከዲያቢሎስ አገዛዝ ነው፡፡
ቅበላ በተለይ የነነዌ ጾም እንዳለቀ ዐቢይ ጾም /ጾመ ሁዳዴ መስከረም አንድ ቀን በታወጀው መሠረት ቀናት ሲቀረው መናንያን፣ ካህናትና ምእመናን ጾሙን ለመቀበል የተለያዩ ዝግጅቶች ያደረጋሉ፡፡ ጾሙ አባ ዲዮስቆሮስ ስለ ዐቢይ ጾም ታላቅነት “ከመ እንተ ብእሲ ለጸዊም በውስተ ገዳም ኃደረ። እምኀበ ዲያብሎስ ተመከረ በኃይለ መለኮቱ መኳንንተ ጽልመት ሠዓረ፤ እንደ ሰው ሆኖ ለመጾም ፵ መዓልት ፵ ሌሊት በገዳመ ቆሮንቶስ ኖረ። ከዲያብሎስ ዘንድ በሦስት አርእስተ ኃጣውዕ ተፈተነ፥ ድል ይነሣልን ዘንድ። ፭ ሺህ ከ፭ መቶ ዘመን ሰልጥነው የኖሩትንና የጨለማ ገዥ የሆኑትን ሠራዊተ ዲያብሎስን በጌትነቱ ሻረልን።” እንዳለው ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን አብነት አድረገን በመጾም በዚህ ዓለም ስንኖር ጥንተ ጠላት ዲያቢሎስን ድል ለማድረግ፣በጾሙ በረከት፣ ጸጋና መንፈሳዊ ኃይል ለማግኘት እንድንበቃ የምናደርገው የዝግጅት ሰሞን ነው፡፡
በቅበላ ሰሞን አባቶቻችን በየገዳማቱና አድባራቱ ለቤተ እግዚአብሔር መገልገያ የሚሆኑ ንዋያትንና መብዓ ያዘጋጃሉ፡፡ስምንቱን የዐቢይ ጾም የሱባዔ ሳምንታት የሚያሳልፉበትን ቦታ ይመርጣሉ፡፡ ለጸሎት የሚያግዟቸውን መጻሕፍት ያዘጋጃሉ፡፡
በጾም፣ በጸሎት፣ በምጽዋት ለማሳለፍ ዕቅድ ያወጣሉ፡፡ ጥሉላት(የእንስሳትና የዓሣ ሥጋ፣የእንስሳት ውጤቶች) ምግቦችን ካስፈለጋቸው ለህሊናቸው ዕረፍት ለመስጠት በመጠኑ ይመገባሉ ጾመው ለማበርከትና ዋጋ ለማግኘት፡፡ በከተማና በገጠር የሚገኙ ምእመናንም ጧፍ፣ዕጣን፣ዘቢብ ፣አልባሳት ሲገዙ ይሰነብታሉ፡፡ አልፎ አልፎም ጾሙን በንጹህ ህሊና ለመጀመር ከአበ ነብሳቸው ጋር ይወያያሉ፡፡ “ወኢትፍራሕ ተጋንዮ በእንተ ኃጢአተከ ኃጢአትህን ለማመን ለመናገር አትፍራ፡፡” እንዳለ ሲራክ 3፡18፡፡ የበደሉ ማሩኝታ የተጣሉም ይቅርታ ይጠይቃሉ ፡፡ ነግቶ ለኪዳን፣ ቀኑን ለቅዳሴና ለሠርክ ጸሎት ለማወል ያቅዳሉ፡፡ መዝሙር ቤቶችም የበገናና ዘለሰኛ መዝሙራትን ያሰማሉ፡፡
ዛሬ ዛሬ ግን ቅበላ ሲባል በአብዛኛው አዕምሮ የሚከሰተው ከሰባው አርዶና አወራርዶ አሊያም ልኳንዳ ቤት ተሰልፎና ታድሞ፣ጥሉላት ምግቦችን በዓይነት አሰልፎ፣ ጠጅ (አልኮል) ተጎንጭቶ፣ከመጠን ያለፈ ደስታ ፈጥሮ ጾሙን መቀበል ሆኗል፡፡ ቅዱስ ጴጥሮስም በመልእክቱ 1ኛጴጥ 5፡8 “በመጠን ኑሩ ንቁም፥ ባላጋራችሁ ዲያብሎስ የሚውጠውን ፈልጎ እንደሚያገሣ አንበሳ ይዞራልና” እንዳለው ከመጠን ያለፈ ማንኛውም ደርጊት ለፈተና ብሎም በዲያቢሎስ ሊያስማርከን ይችላል፡፡
አንድ መምህር ሲያስተምር የሰማሁት ሴትየዋ በቅበላ ብዙ የጥሉላት ምግቦችን አዘጋጅታ ስትመገብ ሰንብታ ጾሙ ሲገባ ምግቡ ሳያልቅ ይቀራል፡፡ አላስችል ብሏት በጾሙ የመጀመረያ ሳምንት የተረፈውን ምግብ ትመገባለች፡፡
ይህችን እናት የህሊና ወቀሳ እረፍት ነሳት ለአበ ነብሷ(ለንስሀ አባቷ) መንገር ጥሩ አማራጭ እንደሆነ ተረድታ ያደረገችውን ነገረቻቸው፡፡ አበ ነብሷም አስተምረው ቀሪውን ጾም በተገቢው ሁኔታ እንድትጾም መክረው ይሸኟታል፡፡ ጾሙ ሊያልቅ ሲቃረብ “ክፉ ባልንጀርነት መልካሙን አመል ያጠፋል።” እንዳለ ቅዱስ ጳውሎስ 1ቆሮ 15፡33 ከማይጾሙ ጓደኞቿ ጋር በመዋሏ የጥሉላት ምግብ ትመገባለች፡፡ አሁንም ከህሊና ወቀሳ መዳን ስላልቻለች ለአበ ነብሷ ለመናገር ወስና ነገረቻቸው፡፡አበ ነብሷም የሴትየዋን ስም ጠርተው “ምነው! ጾሙ ሲገባ አላስገባ አሁን ሊወጣ ሲል አላስወጣ አልሽ ፡፡ ”አሏት ይባላል፡፡
ጾም አቀባበል የሚደረግለት መንፈሳዊነትን ባለቀቀ መልኩ በመጠኑ ሲሆን፤በመጾማችን ድል የምናደርግበት፣በመንፈስ የምናድግበት፣የቤተክርስቲያን ልጅነታችንን የምናረጋግጥበት(ቀኖናና ሥርዓቷን ስለምንጠብቅ) ይሆናል፡፡
ስለዚህ ዝግጅታችን ምን ይሁን?
ጾሙን ተቀብለን፤ ጾመን፣ጸልየን፣መጽውተን ሰግደን ዋጋ እንድናገኝ እግዚአብሔር ይርዳን።
ጥር 26ቀን 2010ዓ.ም
መምህር ቀሲስ ሳሙኤል ተስፋዬ