መጥምቀ መለኮት ቅዱስ ዮሐንስ

መጥምቀ መለኮት ቅዱስ ዮሐንስ ቅዱስ ገብርኤልና አባቱ ዘካርያስ ትንቢት የተናገሩለት፤ ከሕፃንነቱ ጀምሮ እግዚአብሔርን ያገለገለ፤ በፍጹም ልቡ ዓለምን የናቀ፤ ከተድላዋና ከደስታዋም የተለየ፤ አምላክን ለማጥመቅ የታደለ ሐዋርያ፣ መምህር፣ ሰማዕት፣ ባሕታዊ፣ ነቢይ፣ ጻድቅ ነው፡፡

ሊቁም ከመላእክት፣ ከነቢያት፣ ከካህናት፣ ከሐዋርያት መካከል እንደርሱ መለኮትን ለማጥመቅ የተመረጠ አለመኖሩን በመጥቀስ ‹‹… ዮሐንስ ከማከ ሶበ ፈተዉ ወጽሕቁ፤ እሳተነዳዴ ኢተክህሎሙ ያጥምቁ፤ ራጉኤል በትጋሁ ወኢዮብ በጽድቁ፤ … ዮሐንስ ሆይ! ራጉኤል በትጋቱ፣ ኢዮብምበጽድቁ ቢመኙም ኾነ ቢጨነቁ እንደ አንተ የሚነድ እሳትን (መለኮትን) ሊያጠምቁ አልተቻላቸውም›› ሲል ታላቅነቱን መስክሮለታል (መልክአ ዮሐንስ መጥምቅ፣ ለአዕይንቲከ)፡፡

ዮሐንስ ማለት ‹‹እግዚአብሔር ጸጋ ነው›› ማለት ነው፡፡ ቅዱስ ወንጌልም መጥምቀ መለኮት ዮሐንስን ፍሥሐ ወሐሴት (ተድላና ደስታ) ይለዋል፤ ወላጆቹ በእርሱ መወለድ ተደስተዋልና (ሉቃ. ፩፥፲፬)፡፡ በቅዱስ ሉቃስ ወንጌል ምዕራፍ አንድ፣ ከቍጥር አንድ ጀምሮ እንደ ተገለጸው ካህኑ ዘካርያስ እና ሚስቱ ቅድስት ኤልሳቤጥ የእግዚአብሔርን ትእዛዝ ዅሉ በመፈጸም ያለ ነቀፋ የሚኖሩ ጻድቃን ነበሩ፡፡ ኤልሳቤጥም መካን ነበረችና ልጅ አልነበራቸውም፡፡ ልጅ ይሰጣቸው ዘንድም እግዚአብሔርን ዘወትር ይማጸኑት ነበር፡፡

ካህኑ ዘካርያስ ወደ ቤተ መቅደስ ገብቶ ዕጣን በማሳረግ ላይ ሳለም የእግዚአብሔር መልአክ በዕጣኑ መሠዊያ ቀኝ ቆሞ ጸሎቱ እንደ ተሰማና ሚስቱ ቅድስት ኤልሳቤጥ እንደምትወልድ፤ ስሙንም ዮሐንስ እንደሚለው፤ በመወለዱም ብዙዎች እንደሚደሰቱ፤ ልጁም በእግዚአብሔር ፊት ታላቅ እንደሚኾን፤ የወይን ጠጅ እና የሚያሰክር መጠጥ እንደማይጠጣ፤ እንደዚሁም ከእናቱ ማኅፀን ጀምሮ መንፈስ ቅዱስ እንደሚሞላበት ነገረው፡፡

ካህኑ ዘካርያስም መልአኩን ‹‹እኔ ሽማግሌ ነኝ፤ ሚስቴም አርጅታለችና ይህን በምን አውቃለሁ?›› አለው፡፡ መልአኩም ‹‹እኔ በእግዚአብሔር ፊት የምቆመው ገብርኤል ነኝ፤ እንድናገርህም ይህችንም የምሥራችእንድሰብክልህ ተልኬ ነበር፡፡ እነሆም በጊዜው የሚፈጸመውን ቃሌን ስላላመንህ ይህ ነገር እስከሚኾን ቀን ድረስ ዲዳ ትሆናለህ፤ መናገርም አትችልም›› አለው፡፡

ከውጪ ቆመው ጸሎት ሲያደርጉ የነበሩት ሕዝብም ዘካርያስን ከቤተ መቅደስ እስኪወጣ ይጠብቁት ነበር፤ በመዘግየቱም ይደነቁ ነበር፡፡ ከቤተ መቅደስ በወጣም ጊዜ ሊያናግራቸው ባለመቻሉ ይጠቅሳቸው ነበር፡፡ በኹኔታውም በቤተ መቅደስ ራእይ እንዳየ አስተዋሉ፡፡ እርሱም ድዳ ሆኖ ኖረ፡፡ የማገልገሉም ወራት ሲፈጸም ወደ ቤቱ ሔደ፤ ከሁለት ቀን በኋላም አረጋዊቷ ቅድስት ኤልሳቤጥ ፀነሰች፡፡ ቅድስት ኤልሳቤጥም በመካንነቷ ከሰዎች የሚደርስባት ሽሙጥ ተወግዷላታልና ‹‹እግዚአብሔር በዚህ ወራት ከሰው ስድቤን ያርቅ ዘንድ እንዲህ አደረገልኝ›› ስትል ለአምስት ወራት ተሸሸገች፡፡

የመውለጃዋ ቀን ሲደርስም ዘመነ ብሉይ ሊፈጸም፣ እግዚአብሔር ሰው ሊኾን (በሥጋ ሊገለጥ) ስድስት ወራት ሲቀረው፣ ሰኔ ፴ ቀን ንዑድ፣ ክቡር የኾነው መጥምቀ መለኮት ቅዱስ ዮሐንስ ተወለደ፡፡ ዘመዶቹ ስሙን በአባቱ መጠርያ ‹ዘካርያስ› ሊሉት ቢወዱም እናቱ ግን ‹‹ዮሐንስ ይባል›› አለች፡፡

የመልአኩን የብሥራት ቃል ባለመቀበሉ አንደበቱ ተይዞ የነበረው ካህኑ ዘካርያም ስሙ ‹ዮሐንስ› ይባል ብሎ ሲጽፍ አፉ ተከፈተ፤ አንደበቱም ተፈታ፡፡ በመንፈስ ቅዱስ ተቃኝቶም ‹‹… አንተ ሕፃን ሆይ! የልዑል ነቢይ ትባላለህ፤ መንገዱን ልትጠርግ በጌታ ፊት ትሔዳለህና፡፡

የኀጢአታቸው ስርየት የኾነውን የመዳን ዕውቀት ለሕዝቡ ትሰጣለህ፡፡ ይህም ከላይ የመጣ ብርሃን በጐበኘበት በአምላካችን ምሕረትና ርኅራኄ ምክንያት ነው፡፡ ብርሃኑም በጨለማና በሞት ጥላ ተቀምጠው ላሉትያበራል፤ እግሮቻችንንም በሰላም መንገድ ያቀናል፤›› በማለት የቅዱስ ዮሐንስን ነቢይነት እና አጥማቂነት፣ እንደዚሁም የክርስቶስን የማዳን ትምህርት አብሣሪነት የሚመለከት ትንቢት አስቀድሞ ተናገሯል (ሉቃ. ፩፥፶፯-፸፱)፡፡

ቅዱስ ዮሐንስ ሰኔ ፴ ቀን የተወለደበት፤ መስከረም ፩ ቀን ቃል ኪዳን የተቀበለበት፤ መስከረም ፪ ቀን በሰማዕትነት ያረፈበት፤ ጥር ፲፩ ቀን ጌታችንን ያጠመቀበት፤ የካቲት ፴ ቀን ራሱ የተገኘችበት፤ ሚያዝያ ፲፭ ቀን ራሱ ያረፈችበት (ነፍሱ የወጣችበት)፤ ሰኔ ፪ ቀን ደግሞ ፍልሰተ ዐፅሙ (ዐፅሙ የፈለሰበት) በዓል በቤተ ክርስቲያናችን በየዓመቱ ይከበራል፡፡ (ገድለ መጥምቀ መለኮት ቅዱስ ዮሐንስ )

የመጥምቀ መለኮት ቅዱስ ዮሐንስ ገድልና ዕረፍቱ ይቀጥላል

ምንጭ፦ መጽሐፈ ስንክሳር፣ ሰኔ 30ቀን፤ የሉቃስ ወንጌል አንድምታ ትርጓሜ፣ ሉቃ. 1:1-8